Tuesday, December 15, 2015

የፍርሃት ግንብ ይደርመስ>> ከእድሜ ልክ የህሊና እስረኛው ፣ አንዷለም አራጌ!

አቤጋ ጎራው's photo.
ፀጉር አስተካካይ ወጣት ነች ፀጉሩን እያስተካከለችው ላለው ጓደኛዬ ‹‹አሁንስ እሰው አገር ተሰድጄ ብኖር ይሻለኛል›› ትለዋለች፡፡ አጠገቡ ያለ ሌላ ተስተካካይ ‹‹ይኽም የሰው አገር ስለሆነ ሌላ አገር መሄድ አያስፈልግሽም፡፡›› ይላታል፡፡ ይኸን መሰል አባባሎች ሕዝቡ በአገሩ ላይ ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጠ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡

የሃገራችን ሁለንተናዊ መስተጋብር መስመር ይይዝ ዘንድ ፍርሃት ከኢትዮጵያ ምድር ይወገድ፡፡ የፍርሃት ግንብ ይደርመስ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ በአፈ ሙዝ ወይንም በስለላ መዋቅር አስገዳጅነት አሊያም ከስራ በማፈናቀል እና በአያሌ የመብት ጥሰቶች የሚፈፀመው የአፈናና የዘረፋ ተግባርይብቃ፡፡ አንድ አማካኝ መንገድ አለ፡፡ ፍርሃት ሞቶ የሚቀበርበት፡፡ የፍትህ አደባባይ፡፡ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር እንደ አባይ ጅረት ያለማቋረጥ ይፍሰስ፡፡ ፍትህን ሲያከብሩ መሪዎቻችንም$ ከፍርዓት ማዕበል ነፃ ይወጣሉ፡፡ ፍትህ ሲኖር ሕዝብ የመረጠው መንግስት ይመሰረታል፡፡ ፍትህ ሲሰፍን የሰው ልጅ ክብር በኢትዮጵያ ምድር እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራል፡፡ እንደ ሃይለኛ ጅረትም ይፈሳል፡፡ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር ሲሰፍን የፍርሃት ግድብ ይደረመሳል፡፡ ፍርሃት ከየኢትዮጵያዊው ልብ እንደ ማለዳ ጤዛ ይተናል፡፡ አዎ! ፍርሃት ከኢህአዴግአውያን ልብ እንደ ጤዛ ይትነን፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአፈ-ሙዝ አንበርክከው ለመግዛት የሚያሳሙት ቅዥታቸውም እንዲሁ አውሎ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ይወገድ፡፡ ያለፍትህ ነፃነት የለም፡፡ ያለነፃነት ልማት፣ ሰላም፣ ወንድማማችነት የቀን ቅዥት ነው፡፡ ከአምባገነኖች ጋር ተሞዳሙዶ መልማትም ሆነ ፍትህ ማግኘትም የዚያኑ ያህል የቀን ቅዠት ነው፡፡ ፍትህ እንዲሰፍንና ያልተወለዱ ልጆቻችንም ጭምር ከአፈና ለመታደግ ዛሬ ከእያንዳንዳችን ልቦና ፍርሃት ጥፍፍ ብሎ ይውጣ፡፡ እያንዳንዳችን ለሁሉም መብት ሁሉም ለእያንዳንዱ ይታገል፡፡ ኢትዮጵያ ለውስጥ ነፃነቱ ዘብ የሚቆም የጀግና፣ የፍትህ ናፋቂ እና የፍትህ ባለቤት የሆነ የታላቅ ሕዝብ አገር እንድትሆን ፍርሃት ሞቶ ይቀበር፡፡ ፍትህ በተራሮቻችን ጫፍ ላይ ይምቦግቦግ፡፡ ከዚያ ወንድማማችነት ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ያብባል፡፡ ያን ጊዜ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ደረጃ እየገሰገስን ነው እያልን ስኳር እንደ ሃሽሽ በድብቅ በወረቀት ተጠቅልሎ የሚሸጥበት ዘመን ያከትማል፡፡ የዛን ጊዜ ሚሊዬኖች ሬሽን ካርድ ይዘው በኢትፍሩት አይሰለፉም፡፡ ያኔ ለሚሊዬን ኢትዮጵያውያን የስንዴ ምጽዋት መጠየቅ ይቀራል፡፡ ያን ጊዜ ፍቅር በሚያፈረጥመው ክንዳችን፣ ፍትህ ላይ በሚገነባው ውስጣዊ ነፃነታችን በደምና በአጥንታችንም ጭምር የምንወዳትን ሃገራችንን እንገነባታለን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን የቀጣይ ትውልዶች ሁሉ ትምክህትን እንድትሆን እናደርጋታለን፡፡ አዎ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሀይለኛ ጅረት ለዘላለም ይፍሰስ፡፡

No comments:

Post a Comment