በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን የውጪ ጉዳይ
ሚኒስትር ከነበሩት አቶ አክሊሉ ሐብተወልድ ጋር በቅርበት የመስራት ዕድል አጋጥሟቸው የነበሩት ጋዜጠኛው ዘውዴ ረታ ከጋዜጠኝነት ሞያቸው ባሻገር አገራቸውን በአምባሳደርነት ማገልገላቸውን
በመጠቀም ያገኟቸውን ሰነዶች፣ልምዶች፣የአይን እማኝነታቸውን ፣የተለዋወጧቸውን ደብዳቤዎች በመጠቀም ሶስት ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸውንና
ከፍተኛ የምርምር ስራ የተደረገባቸውን ጠብሰቅ ያሉ የታሪክ መጻህፍት አበርክተዋል፡፡
--የኤርትራ ጉዳይ
--ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ
--የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግስት የዘውዴ ዘመን አይሽሬ ስራዎች ናቸው፡፡
በቅርቡ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ታሪክ ላቅ ያለ ቦታ በሚሰጧቸው በአቶ ከተማ
ይፍሩ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ መጀመራቸውን ተናግረው ነበር፡፡ዘውዴ አጼ ኃይለ ስላሴን በዋናነት ኤርትራን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ
ጋር በፌዴሬሽን ለማዋሃድ የሄዱበትን ርቀት በማድነቅ አሁንም ሁለቱ አገራት ወደቀደመው አንድነታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ማድረጋቸውንም
ተናግረው ነበር፡፡
‹‹በትክክል መቼና እንዴት የሚለውን አላውቅም›› የሚሉት አምባሳደሩ ሁለቱ አገራት አንድ አይነት
ታሪክ፣ባህል፣ሃይማኖት፣ስነ ልቦና ያላቸው በመሆኑ በአንድነት ቢቆሙ የበለጠ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡እናም አሁን ያለው ሁኔታ ይህንን
ለማድረግ ባይፈቅድም ሁኔታዎች ሲቀየሩ ነገሮች ይለወጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ››ብለውም ነበር፡፡ዘውዴ ረታ ብዙ ህልምና ተስፋ እንደሰነቁ
ባሳለፍነው ሳምንት በድንገት ለንደን ውስጥ መንገድ ላይ እየሄዱ ወድቀው መሞታቸው ተሰምቷል፡፡የ71 ዓመቱ ዘውዴ እጅግ ተግባቢ፣ሚዛናዊና
ቅንነትን የተሞሉ በጎ ኢትዮጵያ እንደነበሩ ወዳጆቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ከዘውዴ ቀደም ብሎ በተመሳሳይ መልኩ በድንገት ለህልፈተ
ህይወት መዳረጉ የተሰማው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ነው፡፡
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በማስታወቂያ እና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ
ጋዜጠኝነት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል፡፡
በነፃው ፕሬስ ውስጥ የአክፓክ አሳታሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ፀጋዬ ገብረመድህን
አርዓያ ና ስንሻው ተገኝ በሚባሉ የብዕር ስሞች የማይጠገቡ ፅሁፎችን ጦቢያ በተሰኘ
መጽሔት ሲያስነብቡን ቆይተዋል፡፡
"አጥፍቶ መጥፋት" የሚል በጊዜው ብዙ የተነበበ እና ያወዛገበ መጽሐፍም ፀሐፊ ናቸው፡፡ እኚህ በስራቸው ታላቅ መሆን የቻሉ ሰው በድንገት አረፉ የሚለው ዜና ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡
ህልፈታቸውን የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ማስታወቂያ እና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ውስጥ ሲሰሩ የስራ ባልደረባቸው
(አለቃቸው) የነበረው ጋዜጠኛ እና ደራሲ በዓሉ ግርማ እንዴት እንዳለፈ የሚያውቁትን ያህል ሳይነግሩን ወይም ሳይፅፉልን
ማለፋቸውን ስናስብ ነው፡፡ ስለ በዓሉ ህልፈት ምስጢር ፍቺ የተፃፉ ጽሁፎች ሁሉ የጋሽ ሙሉጌታን ስም ያነሱ ነበር፡፡ ብዙ ምስጢር እንደሚያውቁም ይጠቁሙ ነበር፡፡ በእርሳቸው፣ ገዳሙ አብረሃ እና በዓሉ መካከል ስላለው ፉክክር እና ቅራኔ ዝርዝር ይተረኩ ነበር፡፡
የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስርዓተ ቀብር ወዳጅ ዘመዶቻቸው
በተገኙበት በአሜሪካ ተፈጽሟል፡፡ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ፣ዶክተር ሽመልስ ተ/ጻድቅና የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት የጀርባ አጥንት የነበሩት
ባለሃብቱ አቶ አቤሴሎም ይህደጎም ያረፉት ከሰሞኑ ነበር፡፡ ኢቴኒኮ በአምስቱ የኢትዮጵያ እንቁ ልጆች ህልፈት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ለሞያ
ባልደረቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡
No comments:
Post a Comment