በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተደርገው በቅርቡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኬንያው ፕሬዘዳንት ያስገቡት ዲና መፍቲ ከኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ጋር በተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡አስገራሚ ምለሾችን አምባሳደሩ የሰጡበትን ቃለ ምልልስ ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ ይመለከቱት ዘንድ ግብዣዬ ነው፡፡ዲና በኢንተርቪያቸው
--መለስ ዜናዊ የግል መኪናም ሆነ ቤት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል
-በኬንያ በስደት የሚገኙት ጋዜጠኞች ‹‹ጋዜጠኞች ›› አለመሆናቸውን ገልጸዋል
--ኢትዮጵያ ነጻ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በየአምስት አመቱ የምታከናውን ዴሞክራሲያዊት አገር ናት ብለዋል
ጥያቄ -- ወደ ዱባይ ያቀና ነበረው የኡሁሩ ኬንያታ ጄት ወደ መነሻው እንዲመለስ የመደረጉ ምክንያት ኢትዮጵያ መሆኗ ከታወቀ በኋላ ለጥያቄ በኬንያ ሃላፊዎች ተጠርተው ነበር--
ዲና --ከየትኛውም ወገን ጥሪ አልቀረበልኝም፡፡ከምገኝባት አገር ሰዎች ጋር ተገናኝቼያለሁ ይህ ደግሞ በዴፕሎማሲው መስክ የተለመደ ነገር ነው፣ ስለዚህ ጥሪ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡
ጥያቄ --ኢትዮጵያ ግን የፕሬዘዳንቱን ጄት አስቁማለች?
ዲና --በዚህ ዙሪያ አስተያየት አልሰጥም፡፡
ጥያቄ --ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ረዘም ያለ ድንበር ብትጋራም አልሻባብን ማስፈራት የቻለች ትመስላለች፡፡ኬንያ ማድረግ የተሳናት ኢትዮጵያ ግን ማድረግ የቻለችው ነገር ምንድን ነው?
ዲና --የትኛውም አገር በአፍሪካም ይሁን በምዕራቡ አለም የሚገኝ ሽብርተኝነትን አጥፍቺያለሁ ማለት አይችልም፡፡በአንጻራዊነት ኢትዮጵያ ግን ስኬታማ ሆናለች፡፡ምክንያቱም በደህንነቱና በህዝቡ መካከል ጥሩ የሆነ ትብብር በመኖሩ ነው፡፡ህዝቡ ጠቃሚ የሆነን ኢንፎርሜሽን በመስጠቱ የሽብርተኝነት ህዋሶች እንዲጋለጡና እንዲጠፉ አድርጓል፡፡
ኬንያም እየተገበረች የምትገኘው ፍልስፍናም ተመሳሳይ ነው፡፡በኒዩምባ ኩሚ እያንዳንዱ ዜጋ የደህንነት ሰራተኛ ነው፡፡መንግስትም በማዳራሳ ጥሩ የሚባል ግኑኝነት ከሐይማኖት መምህራን ጋር አለው ይህም የእስልምና አስተምህሮ አክራሪነትን እንደማያበረታታ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የጸጥታ ሰራተኞች የአገራቸውን ደህንነት ከምንም ነገር በላይ እንዲያስቀድሙ በአርበኝነት አስተምህሮ እንዲጠመቁ በመደረጋቸው በሽብርተኝነት አስተምህሮ ሊበላሽ አይችልም፡፡
ጥያቄ -በቅርቡ በኬንያና ኢትዮጵያ የጋራ ወሰን አካባቢ ዘራፊዎች በኢትዮጵያ ወራሪዎች ኬንያን አጥቅተዋል፡፡ለእንዲህ አይነት ድርጊት ኬንያ ኢትዮጵያዊያኑን በማጥቃት የአጸፋ ምላሽ መስጠት አለባት?
ዲና -- የወሰን አካባቢ ግጭቶች ሁለቱ አገራት የሚገኙበትን አስደሳች ሁኔታ አያንጸባርቁም፡፡ይህ በኬንያ በሚገኙ ጎሳዎችና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ጎሳዎች ሊያጋጥም ይችላል፡፡ለማንኛውም የድንበር አካባቢ ግጭቶችን ሁለቱ መንግስታት በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችን ትርጉም ባላቸው የልማት እንቅስቃሴዎች በማሳተፍ ሊያስወግዱ አልያም ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡
ጥያቄ --በቅርቡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሐይሎች 16 ኪሎ ሜትር ወደ ኬንያ በመግባት በዚያ የሚገኘውን የፖሊስ ጣብያ ተቆጣጥረው ነበር ….
ዲና -ይህንን ክስ የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ በግልጽ አስተባብለዋል፡፡ኢትዮጵያ ከአል ሻባብ ጋር በምታደርገው ጦርነት ኬንያ የኢትዮጵያ ጠንካራ ተባባሪ ናት፡፡በታሪክ ውስጥ ሁልግዜም ለኬንያዊያን ቅርብ ነን፡፡የውስጥ ችግር በነበረን ወቅት ኬንያ ለኢትዮጵያ ስደተኞች የሰላም ደሴት በመሆን አገልግላለች፡፡ስለዚህ በኢትዮጵያ ወታደሮች በኬንያ ላይ የተደረገ ወረራ ከዚህ በፊት እንዳልነበረ ሁሉ ወደፊትም አይኖርም፡፡
ጥያቄ--የኬንያ የንግድ ሰዎች በኡጋንዳ ፣ሩዋንዳና ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ መጠን ይገኛሉ፡፤ለምንድን ነው ወደ ኢትዮጵያ የማይሄዱት ? ኢኮኖሚያችሁ ክፍት ወይስ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው ?
ዲና --የእኛ ኢኮኖሚ ለሁሉም ኢንቨስተር ክፍት ነው፡፡ ብዙ የኬንያ የንግድ ሰዎች በኢትዮጵያ በመገኘት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በኬሚካል ኢንዳስትሪ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰዋል፡፡በእርግጥ ኬንያዊያኑ ይህንን በማድረግ ከግብጽና ሱዳን በመለጠቅ ሶስተኛ ናቸው፡፡
ጥያቄ --ብዙ ኢትዮጵያዊያን በኬንያ በህገ ወጥ መንገድ በመግባታቸው ታስረዋል፣ሌሎች በሊቢያ ለመሞት አሁንም እየሄዱ ነው የተወሰኑት ደግሞ በአይ ኤስ አይ ኤስ ተገድለዋል…
ዲና --እነዚህ የታሰሩት በሰው አዘዋዋሪዎች በውጪ አገር ገነትን የመሰለ ህይወት ትኖራላችሁ ተብለው ተስፋ የተገባላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ በአብዛኛው ወጣትና ከገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ናቸው፡፡የሚበዙት ኢትዮጵያዊያን ግን በአገር ውስጥ እየተፈጠረ በሚገኘው ዕድል በመጠቀም ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት አገር በመሆኗ ነጻና ተአማኒነት ያለው ምርጫ በየአምስት አመቱ የምታደርግ በመሆኗ ወታደራዊ አገዛዝ የሰፈነባት ናት ማለት አይቻልም፡፡
ጥያቄ -ብዛት ያላቸው ጋዜጠኞች በኬንያ በስደት ላይ ይገኛሉ፣ በዚህ ላይ ስድስት የሚታወቁ ጦማሪዎችና ሶስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ ናቸው አይደለም እንዴ አምባሳደር ?
ዲና --የኢትዮጵያ የሚዲያ ነጻነት ምህዳር በጣም ለጋ ነው፡፡የተጀመረውም በ1991 ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣ ነው፡፡ስለዚህ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ነገር ግን የማንፈቅደው ነገር ምንድን ነው ሰዎች በጋዜጠኝነት ካባ ተሸፍነው ዜጎችና ጎሳዎችን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እንዳያነሳሱ ነው፡፡ስለዚህ በኬንያ የሚኖሩት እውነተኛ ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡የስድስቱ ጦማሪያንና የሶስቱ ጋዜጠኞች ጉዳይ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኝ በመሆኑ አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡
ጥያቄ -- መለስ ዜናዊ ከሞቱ ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡እንዳጣችሁት ይሰማችኋል ?
ዲና --እንደ ህዝብ በጣም አጥተነዋል፡፡ምክንያቱም እርሱ የኢትዮጵያ የህዳሴ አባት ነበር፡፡የግሉ መኪና እና መኖሪያ ቤት ሳይኖረው የሞተ ብቸኛ አፍሪካዊ መሪ እርሱ ነው፡፡ መለስ አገልጋይ መሪ ነበር፡፡የቀድሞው መለስ የራሱን ስብእና ከመገንባት ይልቅ የስርዓት ሰው ነበር፡፡ጠንካራ ስርዓትን ዘርግቶ በማለፉም ከእርሱ ስንብት በኋላም በእርሱ ስርዓት እየሄድን እንገኛለን፡፡
ጥያቄ --ኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የኤሌክትሪክ ባቡር ግንባታን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ይህ በኬንያ ከሚገኘው በመጠኑ የሚተልቅ ቢሆንም ወጪው አነስተኛ ነው፡፡ይህ እንዴት የሚቻል ሆነ ?
ዲና --በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅና ዝርዝር መረጃ የለኝም፡፡ምክያቱም የሰለጠንኩበት ዘርፍም አይደለም፡፡ነገር ግን እንደ አገር ሙስናን መቀነስ በመቻላችን በአስገራሚ ሁኔታ ከአንዳንድ ፕሮጀክቶች ወጪ መቀነስ ችለናል፡፡
ጥያቄ --አዲስ አበባ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ የሚያስችሏትን (እንደ ባቡር ያሉ) መኪኖች አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ይህ በአውሮፓ አገሮች በጣም የተለመደ ነው፡፡ናይሮቢ ከዚህ መውሰድ የምትችለው ነገር ምንድን ነው
ዲና --አዎን ላለፉት ሶስት ወራቶች በሌሎች ከተሞች ጭምር የሙከራ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
ናይሮቢም አቅሙ ያላት በመሆኑ የትራፊክ መጨናነቁን ለመቀነስ ሐሳቡን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባታል ፡፡ በአዲስ አበባ ሙከራው የትራፊኩን መጨናነቅ ሲቀንስ ተመልክቻለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment