Tuesday, June 2, 2015

ከዚህ በላይ ሰላማዊነት ይኖር ይሆን?

እንደ አንድ አባት አሳድገው ትውልድን መቅረጽ ወደሚያስችላት የመምህርነት ሞያ ያደረሷትና ታናሽ እህቷ (እስከዳር አለሙ)ከዚህ ቀደም እንደተረከችልን ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት የዘለቀውን የጋዜጠኝነት ተሰጥኦዋን አውጥታ ለግፉአን ድምጽ እንድትሆን ያበረቷት ልጃቸው ጠመኔ ጨብጣ ከምታስተምርበት አስኳላ በመንግስት ሐይሎች ታፍና ተወስዳ በመንግስት አፍ ‹‹የአገሪቱን መሰረተ ልማቶች የማፈራረስ ትዕዛዝ ተቀብላ በቁጥጥር ስር ስለ መዋሏ ሲነገር አቶ ዓለሙ ጎቤቦ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ‹‹አባትነት›› ለሆነላቸው ሁሉ የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ አቶ ዓለሙ ለጋዜጠኛና መምህርት ልጃቸው አባት ከመሆናቸው ባሻገር በሞያቸው ጠበቃ ናቸው፡፡የአገሪቱ ህገ መንግስት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን በተመለከተ ምን እንደሚል ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ተጠርጣሪዎች ጠበቃ ሳያገኙ ቃል ያለመስጠት መብት እንዳላቸው ይህንኑ መብት የማክበር ግዴታ ፖሊስ እንዳለበት ጠበቃው ይረዳሉ፡፡ ልጃቸው የምትገኝበትን ሁኔታ እንደ አባት የማወቅ መብት ቢኖራቸውም በሞያቸው ጥብቅና ሊቆሙላት የሚችሉ መሆናቸውም የአቶ ዓለሙን መብት ድርብርብ ያደርገዋል፡፡ርዕዩት ወደምትገኝበት ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ልጃቸውን በማየት ተስፋ ተሞልተው አመሩ‹‹አባትም ሆኖ ጠበቃ በዚህ ወቅት ርዕዮትን ማየት አትችሉም አሏቸው››፡፡ ለርዕዮት አባትም ጠበቃም ለሆኑት አቶ ዓለሙ ይህ ሊቀበሉት የሚችሉት አልነበረም ግን ህገ መንግስቱን ሌሎችን ለማጥቂያነት የሚጠቀሙበት ጉልበተኞች ምድሪቱን በመቆጣጠራቸው አቶ ዓለሙ ልጃቸውን ለወራት ማየት ሳይሆንላቸው ቀርቷል፡፡ ርዕዮት ፍርድ ቤት ከቀረበች በኋላ አባቷ ጠበቃዋ በመሆን ተከራክረውላታል፡፡ልጃቸውና የህግ ደምበኛቸው ባልዋለችበት እንድትውል ተደርጋ ያልፈጸመችውን እንደፈጸመች ተስላ 14 ዓመት በካንጋሮው ፍርድ ቤት ሲወሰንባት አቶ ዓለሙ በአካል ተገኝተው አስተውለዋል፡፡ ልጃቸውንና ደምበኛቸው ቃሊቲ እንድትወርድ ከተደረገች በኋላ እንዳይጎበኟት የተደረጉባቸው ጊዜያት ቀላል የማይሰኙ ናቸው፡፡የህግ ደምበኛቸው ውላቸውን አቋርጣ ከአሁን በኋላ ጠበቃ አያስፈልገኝም ሳትል ቃሊቲዎች ‹‹ከአሁን በኋላ የፍርድ ሂደቱ ስለ ተጠናቀቀ እንደ ጠበቃዋ ሊጎበኟት አይችሉም ››በማለት እንደ ወላጅነታቸው ብቻ እንዲጎበኟት አድርገዋል፡፡ ርዕዮት ህክምና እንዳታገኝ የተለያዩ ማዕቀቦች ሲጣሉባት፣በምርመራ ወቅት ስለ ደረሰባት የመብት ጥሰት፣ጨለማ ቤት ስለ መታሰሯ አቶ ዓለሙ ደጋግመው ሰምተዋል፡፡ ይህ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ዝም ለማሰኘት የማይፈነቅለው ደንጊያ እንደሌለ በበኩር ልጃቸው ደርሶ ተመልክተዋል፡፡ፍርድ ቤቱ ከጀርባ በሚመራው ሐይል እንደሚዘወር የህይወት ምስክር ናቸው፡፡ አቶ ዓለሙ ቀጣፊዎች፣ሐሰተኞች፣በቀን ሰውን ጨለማ ክፍል ለመወርወር ኬዝ የሚጋግሩ አቃቢያነ ህጎች፣በአንድ የስልክ ጥሪ ፍትህን እንዳልተፈጠረች የሚቆጥሯት ዳኞች ከምንም በላይ ከመሳሪያ በሚወጣ የባሩድ ሽታ ስልጣነ መንግስታቸውን የሚያጥኑ ነፍጠኞች በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት እንደተሰገሰጉ ቢያውቁም ይህ ስርዓት በህዝብ ድምጽ ከስልጣኑ ይወርዳል በማለት በዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ የመድረክ ዕጩ በመሆን ቀርበው ነበር፡፡ የስርዓቱን አስከፊነት በራሱ ቤተሰብ ደርሶ እንደተመለከተ እንደ አቶ ዓለሙ አይነት ሰው ራሱን በማሳመን ‹‹ወደ ምርጫ ፖለቲካ››ሲገባ አክብሮት ሊቸረው ይገባል፡፡ከዚህ በላይ ሰላማዊነትስ ይኖር ይሆን ? የዛሬ ገዢዎች ሐይማኖታቸውን ‹‹ብረት››በማድረግ እንደ እጅ መንሻ ጉልበቶቻችንን በመሳሪያቸው ቢያሰግዱም ከእነርሱ በላይ የአቶ ዓለሙ ሰላማዊነት ድምጽ አውጥቶ ይጣራል፡፡ፍጹም በደል በስርዓቱ የደረሰባቸው ቢሆኑም ህዝብን አምነው የምርጫው ተዋናይ በመሆናቸው መንግስት ከኮሮጆ በሚወጣ ድምጽ አይወርድም በሚሉ ወገኖች ጭምር አክብሮት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ምን አልባት አንድ ቀንም ይህንን ቁርጠኝነት የምንዘክርበት ዕድል ይፈጠር ይሆናል፡፡ ብዙ ክብር ለአቶ ዓለሙ ጎቤቦ

No comments:

Post a Comment