Friday, November 27, 2015

ወደ እስር ቤት ተወርውሮ የተረሳው ኦኬሎ አኳይ ኦቻላ


አንድ የኖርዌይ ዜጋ በውጭ አገር እሰር ቤት ተጥሎ የሞት ፍርድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ለበርካታ ዓመታት እስርቤት ህወቱን እንደሚገፋ መገመት አያዳግትም። የኖርዌጂያን ጆሮ ዳባልበስ ማለት ኦኬሎ አኳይ ኦቻላን በከሳሾቹ ፊት ብቻውን እንዲቆም አድርገነዋል ሲሉ በኖርዌ የጸረ ዘረኝነት ማዕከል ሓላፊ የሆኑት ጠበቃ ሩነ ቤርገሉንድ ስቲን እና ምክታላቸው ኤቪን ኮህን ዳግስ ብላ ለተባለው የኖርዌይ ጋዜጣ አሳወቁ። በ 2009 ቶስቶቨ ሙላንድ እና ዩሽዋ ፍሬንች  በተሳሩበት ወቅት በተከታታይ ይዘግቡ ነበር:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በተከታታይ ለህዝብ ያሳውቅ ነበር። ታዲያ የኦኬሎ አኳይ ኦቻላስ ጉዳይ ለምን  ችላ ተባላ?። ኦኬሎ የኖርዌይ ዜጋ ነው ወደ ኖርዌይ የመጣው በስደት ነው ላለፉት ሁለት ዓመታት በ ኢትዮጵያ በ እስር እየማቀቀ ነው የፍርዱ ሂደት በቅርብ ይጀመራል:: በዚች ምድር ሊረዳው የሚችል ቢኖር እኛው ነን ታዲያ ለምን አንረዳውም? ሚዲያዎች ለምን ጸጥ ረጭ ማለትን መረጡ ሲሉ ይሞግታሉ።
ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ከፍተኛ ጉዳይ ነው። ኦኬሎ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት በ 2003 400  የአኝዋክ ብሔረሰቦች በጥይትና በመጥረቢያ ሲጨፈጨፉ በመቃወሙና ራሱም አደጋ ውስጥ በመውደቁ ነው ለስደት የበቃው። ኦኬሎ ራሱ የአኝዋክ ቤሔረሰብ አባል ነው። በተባበሩት መንግስታት እውቅና ያገኘና በኖርዌይ ዜግነት ያለው ስደተኛ ነው። አራቱ ልጆቹና ባለቤቱ ኖርዌይ ውስጥ ይኖራሉ። እንደ ኦኬሎ እነሱም የኖርዌይ ዜጋ  ናቸው። አሁን ባለቤቱም የትዳር አጋሯን ልጆቹም አባታችውን ትተዋት ከተሰደዱባት አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እስርቤት እየማቀቀ መሁኑን እያወቁ ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ቁጭ ብለዋል፡:
የኢትዮጵያ መንግስት ኦኬሎ ገንዘብ ሰብስቦ ተዋጊ ቡድን ሲመለምል ይዘነዋል በሚል በሽብርተኝነት ክስ ከሶታል። የሺብርተኝነት ክስ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለመምታት በብዛት ይጠቀምበታል። የኦኬሎ ጉዳይም ቢሆን የፈጠራ ክስ ላለመሆኑ ምንም መረጃ የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር አይታወቅም ታይቶም አያውቅም ሲል ዳግስ ብላ የተባለው የኖርዌይ ጋዜጣ ዘግቡአል። ከበርካታ የጦርነት አመታት በሁአላ ኢትጵያ የሰባዊ መብት በሰፊው የሚጣስባት የራሷን ህዝብ የምታሰቃይ በብዛት ጋዜጠኞች የታሰሩባትና የሕግ ሰርዓቱ ለገዥው መንግስት ከለላ የሆነባት አገር ናት ብሏል።

የኖርዌይ ባለስልጣኖች ኦኬሎን ለመጎብኝት ተከልክለዋል:: ይህ ደግሞ በኣገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን የዲፕሎማሲ ስምምነት ህግ የጣሰ ነው። በስቶኮልም የሚገኘው  የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጉዳዩ ግልጽ ያለመሁን ነገር ነው ሲል ጉዳዩን አለባብሶታል። ኖርዌይ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታ ከሚለግሱ አገሮች አንዷ ናት። ምንም  እንኳን እርዳታን ከአንድ ግለሰብ አያያዝ ጋር በቀጥታ ማገናኘት ራሱን የቻለ ችግር ቢኖረውም የኖርዌይ ባለስልጣኖች ጉዳዩን ከዚህ የበለጠ አጠንከረው ሊሄዱበት ይገባ ነበር፡፤ ኦኬሎ እንደ ኖርዌጂያን ዜጋ ከኖርዌይ ውጭ ሃላፊነት ወስዶ ሊያግዘው የሚችል አገር አይኖርም። እኛ ካረዳነው ማስቀያት ወይም ቶርቸር የቀን ከቀን ስራ በሆነባት አገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም አመታት መታሰርን መጠባበቅ ግዴታ ይሆንበታል።
ሁማን ራይትስ ዎችና አመነስቲ ስለ ኦኬሎ ጉዳይ ደወላቸውን እያቃጨሉ ነው። ይሁን እንጂ ሚድያዎች ትኩረት ሊሰጡት ኣልቻሉም ዳግስ ባላ ከተባለው የኖርዌይ ጋዜጣ በስተቀር።  የኖርዌይ ማህበረሰብ ዝምታ ለኦኬሎ ከፍተኛ ጉዳት አለው። የኢትዮጵያ መንግስት በእርዳታ ላይ የቆመ መንግስት ስለሆነ ያልሆነው ዲሞክራት ሰብ አዊመብት ጠባቂ መስሎ መታየት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ዝምታው ይመቸዋል ማለት ነው። የሁሉቱም አገሮች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከህዝቡና ከሚዲያዎች ከፍተኛ ጫና ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን ቢቀርና በ ኦኬሎ ላይ ፈረደ ገምድል አይነት ፍርድ ቢፈረድበት ያስተዛዝበናል በኖርጂያን ዜጎች መካከል ልዩነት አለ እንዴ? ያሰኛል ሲሉ የኖርዌይ የጸረ ዘረኝነት ማዕከል ሓላፊዎች ለዳግ ብላ ሪፖርት አድርገዋል። ሪፖርቱ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ከ 100 ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች ተደግፏል ወይመ ላይክ ተደረጓል፡፡

Wednesday, November 25, 2015

ምስጢር ካወጣህ ቤተሰቦችህን እንፈጃቸዋለን” “ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል


“የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል”
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ በዝዋይ እስር ቤት ለወራት ስቃይ የተፈፀመበት
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ይባላል፤ አርሲ አርባ ጉጉ ተወልዶ አዳማ/ናዝሬት አድጎ፣ በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ተመርቋል፡፡ በ2000 ዓ.ም በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በሲኒየር ካልቸራል ኤክስፐርትነት የስራ መደብ እስከ ሚያዝያ 2003 ሰርቷል፡፡ ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በግልፅ ባልተረዳው ምክንያት የመንግስት ደህንነት ሀይሎች ተያዞ ለ23 ወር በዝዋይ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈፀመበት መቆየቱን ይናገራል፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ከእስራት ሲለቀቅም አንድ ጊዜም እንኳን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ ከወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ጋር ያደረግነውን ቆይታ ተከታተሉን፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ማን ነበር ያሰረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በማለዳ ቤቴ ተንኳኳ፤ ተነስቼ ከፈትኩኝ፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ “ና ውጣ፤ ልብስህን ለብሰህ ውጣ” አሉኝ፡፡ እኔ እናቴ ሞታ ሊያረዱኝ የመጡ መስሎኝ “ምነው ቤተሰብ ደህና አደለም? የተፈጠረ ችግር አለ?” አልኳቸው “ዝም ብለህ ናውጣ” አሉኝ፡፡ ልብሴን ለበስኩኝና ወጣሁ፤ አንቀው መኪና ውስጥ ከተው ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝና 3 ወር አሰሩኝ ከዛም አንድ አመት ከ8 ወር ዝዋይ ማረሚያ ቤት፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- መታሰርህን ለቤተሰብ ተናግረሀል?
ወጣት ተስፋዬ:- ለማንም ሰው እንድናገር አልፈቀዱልኝም፤ መስሪያ ቤቴ አልጠየቀኝም፣ ደሃዋ እናቴ ያለችው ናዝሬት ነው እሷም የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አባቴ አቶ ተካልኝ አስተማሪ ነበር አርባ ጉጉ ላይ ነው በ1985 ዓ.ም በነበረው ግጭት ነው የተገደለው፡፡ ማንም ሳይጠይቀኝ፣ፍ/ቤት ሳልቀርብ 23 ወር ታሰርኩ ልብስ ምግብም የሚያመጣልኝ ሰው አልነበረም፡፡ እናቴም መታሰሬን እንኳ አታውቅም መስሪያ ቤቴም ስኮላርሽፕ አግኝቷል፤ ወደ ውጪ ሃገር ሊማር ሊሄድ ነው የሚባል ነገር ስለነበረ አልጠየቁኝም፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የት ነበር ስኮላርሺፕ ያገኘኸው?
ወጣት ተስፋዬ:- የዛሬ 2 ዓመት አካባቢ የራስመስ ሙንደስን ስኮላርሽፕ አግኝቼ ነበር፡፡ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያና ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶክዮ ባሉ ምሁራን ሪኮመንድ ተደርጌ በጣሊያኑ ፌራሪ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንደተፈታሁ ሄጄ ስጠይቃቸው ብዙዎቹ ጓደኞቼ በጣም ደነገጡ፡፡ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ቅማል ተወርሬ … ባካችሁ ተውኝ … ምንም የሌለ ነገር የለም በጣም ተጎድቻለሁ፡፡ ከማረሚያ ቤት እንደወጣሁ እናቴ ጋ ስሄድ በጣም ደነገጠች፣ በሕይወት ያለሁ አልመሰላትም 23 ወር ሙሉ ከቤተሰብ ስለተለየሁ ግራተጋባች፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- በእስር ወቅት የደረሰብህ ድብደባና ማሰቃየት ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ጀርባዬ ላይ አቃጥለውኛል፣ በብልቴ ላይና በኩላሊቴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብኝ ሽንት ችዬ አልሸናም፣ ሽንቴን መቆጣጠርም አልችልም፡፡ ኩላሊቴንም በጣም ያመኛል፡፡ ውሃ ውስጥ እየነከሩ በጣም ደብድበውኛል፡፡ አሁን ስናገር ያመኛል ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደው ስታስበው ለእስር ያበቃህ ወይም ከመንግስት ጋር ያጋጨህ አጋጣሚ ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- መስሪያ ቤቴ ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፤ በጣም ይከታተሉኛል፡፡ በቢ.ፒ.አር ላይ ስብሰባ በተደጋጋሚ ይጠራ ነበር፡፡ እኔም ሠራተኛ ላይ ተፅእኖ የሚያደርሱ ነገሮች ሲመጡ እኔ አልቀበልም በግልፅ እናገር ነበር፤ ሠራተኛውም እኔን ይደግፋል፡፡ ከመታሰሬ ጥቂት ጊዜ በፊት ገነት ሆቴል ስብሰባ ነበረን፡፡ በዛ ስብሰባ ላይ በጣም ተከራከርኩ፤ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አቶ ፀጋዬ ማሞ የሚባሉ አሰልጣኝ፣ ከውጭ ጉዳይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ከንግድና ኢንዱስትሪም የመጡ ነበሩ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ባለስልጣን ነበሩ፤ እዛ ላይ ሀሳብ አንስቼ ተከራክሬ ነበር፡፡ “የሠራተኛን ሀሳብ ዳይቨርት ያደርጋል” ይሉኝ ነበር፡፡ መቼም ግን ሀሳቤን በመናገሬ ይህን የመሰለ ስቃይ ይደርስብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ “አሸባሪ፣ ግንቦት ሰባት” እያሉ እኔ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ያለምንም ፍርድ በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምረው እያስተኙ አሰቃዩኝ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደዚህ ያሰቃዩህ ምን አይነት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ ነው?
ወጣት ተስፋዬ:- እኔን ጥፋተኛ የሚያስደርግ ምንም መረጃ አላገኙም፣ እኔን አስረው ወደ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ይደውሉ እንደነበር ይነግሩኝ ነበር፡፡ የኢሜይል አድሬሴንም ተቀብለው በርብረዋል ግን ምንም አላገኙም፡፡ እኔ ከማንም ጋር ሊንክ የለኝም ኢሜሌ ላይ የስኮላርሺፕ መልዕክት ካልሆነ በስተቀር ምንም የለውም፡፡ በመስሪያ ቤቴ ሪሰርቸር ነበርኩ፣ በሶሲዮሎጂ ነው የተመረኩት፡፡ ሉሲ የተገኘችበት ሣይት ላይ አፋር፣ ጋምቤላ ብዙ ሳይቶች ሰርቻለሁ፡፡ ከአለቆቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት ሰላማዊ ነው እነሱ ናቸው ስኮላርሽፕ ሪኮመንድ ያደረጉኝ፡፡ አንደኛው ፕሮፌሰር 25 ዓመት ሙሉ እዚህ አገር ሰርቷል፣ አርዲን ያገኘው እሱ ነው፡፡ ሄነሪ ጊልበርት ይባላል፤ እሱም ሪኮመንድ አድርጎኛል፡፡ እኔ በጣም የሚቆጨኝ ደሃዋ እናቴ አረቄና ጠላ ሸጣ ነው ያስተማረችኝ ምን ብዬ ልንገራት እንደዚህ አትጠብቀኝም ከበደኝ፣ አሁን እሷ የምትሰጠኝ ምግብ ራሱ ደምደም አለኝ… (ረጅም ለቅሶ)፡፡ ልጄ በደህናው አይደለም የጠፋው ሞቷል ወይም መኪና ገጭቶታል ብላ ነበር የምታስበው፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የከመታሰርህ በፊት ፖለቲካ ተሳትፎ ነበረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- 1997 ዓ.ም የቅንጅት ደጋፊ ነበርኩ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ በ97 የነበረው ሁኔታ ስንት ሰው አለቀ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር ታውቃላችሁ ምንም የምናደርገው ነገር አልነበረም ፡፡ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ እንደማይቻል ተረዳሁኝ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልሆንኩም፡፡ ከዚህ በኋላ ከምንም ነገር የተገለልኩ ሆኛለሁ፡፡ አንድ ብርጭቆ ሳትሰብር አሸባሪ ስትባል አስብ እንግዲህ አንድ ብርጭቆ እንኳን ሰብሬ አላውቅም ባለኝ እውቀት እንደውም ለእውቀት ነው የምጓጓው እውቀቴን አሳድጌ አገሬን ለመለወጥ ነው የማስበው እኔን ምንም የሚመለከተኝ ነገር የለም አሸባሪም ግንቦት ሰባትም አይደለሁም፡፡ስትደበደብ፣ ስትሰቃይ ያላደረከውን አድርጌያለሁ ትላለህ፤ በርሜል ውሃ ሞልተው ይከቱሃል ያሰቃዩሃል፡፡ አያሳዝንም ይሄ? እንዴት አድርጎ እዚህ አገር ይኖራል? 23 ወር ሙሉ አስረው ማሰቃየታቸው ሳያንስ የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በላይ ሞት የለም ብዬ ነው የነገርኳችሁ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን የት ነው የምትኖረው?
ወጣት ተስፋዬ:- መኖሪያ የለኝም … (ረጅም ለቅሶ)

Monday, November 23, 2015

ETNK weekly report 22 11 2015


.በኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2005 በ አምባገነኑ እና በአረመኔው መለስ ዜናዊ የተፈጸመውን የግድያ እልቂት እናስታውስ፣ ሲሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ጥሪ አቀረቡ


.. 2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ የህዝቡ ድምጽ በቀን ብርሀን በአደባባይ ተዘርፏል በሚል ምክንያት ሰላማዊ ዜጎች ተቃውሟቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስታወቅ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣቸው ብቻ    አሁን በህይወት የሌለው እና በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን (-ህወሀት) ስብስብ እያልኩ የምጠራው የማፊያ እና ወንጀለኛ ድርጅት መሪ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት እንዲፈጸም አግዓዚ ለሚባለው ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ቀጥተኛ የሆነ የግል ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች እንዲያልቁ አደረገ፡፡
አጠቃላይ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫው ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ .. ግንቦት 16/2005 መለስ ዜናዊ ሁሉንም የፖሊስ፣ የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይል አዛዥነቱን በእራሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ በህዝብ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳይካሄድ በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሀገሪቱን መናገሻ ከተማ የፖሊስ እና ልዩ ኃይሉን በማሰማራት የጦር ቀጣና አውድማ አደረጋት፡፡
በቀጣዮቹ ሳምንታት እና ወራት አምባገነኑ እና አረመኔው መለስ በእርሱ አገዛዝ ላይ ተቃውሞ በሚያሳዬው ማንኛውም ዜጋ ላይ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሉ ነጻ እርምጃ እንዲወስድ በግሉ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
.. በግንቦት እና በህዳር 2005 በጨካኙ መለስ የእልቂት ትዕዛዝ ግድያ የተፈጸመባቸው ንጹሀን ዜጎች ቁጥር ቁጥራቸውን አሳንሰው በሚያቀርቡት የመንግስት ባለስልጣኖች እና እራሱ መለስ ባቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን በቀረበው ዘገባ እንኳ 193 ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 763 የሚሆኑት ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ (ትክክለኛው የሟቾች እና የቁስለኞች ቁጥር ግን አጣሪ ኮሚሽኑ ካቀረበው ዘገባም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
እነዚያ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች የመለስን በሸፍጥ የተካሄደ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በመቃወም መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም በመሞከራቸው ምክንያት ብቻ እንደ አውሬ እየታደኑ በየመንገዱ እና በየቤቶቻቸው ውስጥ በግፍ ተገድለዋል፡፡እነዚያ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰማዕት ሆነው አልፈዋል፡፡ .. ህዳር 13/2005 ISIL ጋር አንድ ዓይነት የሆነው ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን በፓሪስ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን እልቂት ፈጽሟል፡፡ ISIL ንጹሀን የፈረንሳይ ዜጎችን እና የሌሎች በፓሪስ ውስጥ ከሚገኙት 15 ሀገሮች ዜጎችን በመፍጀት እስልምናን እጠብቃሁ ብሏል፡፡
የሸክስፒርን አባባል በመዋስ “ሰይጣን ለእራሱ እኩይ ምግባር ሲል ከመጽሀፍ ቅዱስ (ከቁራን) ይጠቅሳል“ ብለዋል፡፡
አልበርት አነስታይን በአንደ ወቅት እንዲህ በማለት አስጠንቅቀው ነበር፣ “ዓለም ሰይጣናዊ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ብቻ አይደለም ለመኖር አስቸጋሪ የሆነች ቦታ የሆነችው፡፡ ሆኖም ግን ስለዚህ ሰይጣናዊ ሁኔታ ምንም ነገር ሳያደርጉ ዝም ብለው በሚመለከቱ ሰዎች ምክንያት እንጅ፡፡”እኔም እንደዚሁ ኢትዮጵያ ሰይጣናዊ ገዥዎች በመኖራቸው ምክንያት አይለደም ለመኖር አስቸጋሪ ሀገር የሆነችው፣ ሆኖም ግን ስለዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ዲያስፖራው ምንም ዓይነት ነገር ባለማድረጋቸው ምክንያት እንጅ እላለሁ ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡


Saturday, November 21, 2015

‹‹ታጋይ ይታሰራል ትግሉ ይቀጥላል፤ ››

የሀብታሙ አያሌው መልዕክት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
በሞት ጥላ መካከል ብሄድ እንኳን ክፉን አልፈራም !!!
********************************************************
የልቤን ምጥ ልፃፈው ብዬ ደጋግሜ ብዕሬን ይዤ ወረቀቱ ላይ ብፅፍም እንደተራበው ወገኔ ሆድ ብዕሬ ባዶ ሆኖ ቀለም አልነጥበው አለ፡፡ በቅሊንጦ ማጎሪያ ቤት ሰማይ ስር ነፍሴ ሀዘን አቆርዝዛ በማይገፉ ቀንና ሌሊቶች ውስጥ ባዘነች፡፡ ለወትሮው ወገኔ እንደከፋው ስሰማ እንደወፍ በርሬ ችግሩን ልጋራው ከመሃሉ እደርስ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የህዝቤ ስቃይ ወደ ሰማይ ጉኖ በጠኔ ሲንበረከክ እንደ ጅብራ ተገትረው በማያንቀሳቅሱኝ ወታደሮች ተከብቤ በጭንቀት እየባዘንኩ ከመጠውለግ በቀር አደርገው ነገር አጣሁ ፡፡ ወይ ሀገሬ!!! ወይ ወገኔ!!! ….. እመነኝ እንዳልኩህ አሁንም እመነኝ … አሁንም እመነኝ !!! እመነኝ ደርግ ወድቋል ኢህአዴግ ይወድቃል፡፡ ዛሬ በአሳሪዎቼ ጡጫ ተደቁሼ፤ ድምፄ በኢትዮዮጵያ ሰማይ ስር ባይሰማም የታገልኩለት እውነት ወደ አደባባይ ወጥቶ ህዝቤ የነፃነት ሻማ እሚጎናፀፍበት ቀን እንደሚመጣ ግን ጥርጥር የለኝም፡፡ የልጄ ናፍቆት የሚስቴ ስቃይና እንግልት የእህቶቼ መባከን እና መሳቀቅ አቅሜን ሲፈታተኑት በማዕከላዊ የስቃይ ማማ ስር ጉዳት ያተረፉት ሁለቱ ኩላሊቶቼ የቀን ከሌት ስቃዬን ሲያረዝሙት የነከስኩት ጥርሴ ጉልበቴ አበርትቶ የነፍሴን መዛል ብሸሽግም… ዛሬ ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የታገልኩለት ህዝብ በረሃብ ጠኔ እየተመታ በሞት ጥላ መንበርከኩን ስሰማ ነፍሴ በውስጤ አለቀች እናም የልቤን ሀዘን እፅፍ ዘንድ ሞከርኩ… ሞከርኩ ግን አቃተኝ…. ጃርት እንደ በላው ዱባ በየቦታው የተፈረካከሰው ፓለቲካችን ዛሬም እርስ በእርስ እየተሸነቋቆጠ ይቀጥላል ወይስ ወገኑን ለመታደግ እንኳ አንድ ይሆናል? ነፍሴ በየእለቱ የምትሟግተኝ ጥያቄ ነው ፡፡ ሳንተባበር ጉልበት አንድ ሳንሆን ኃይል ከወዴት እናገኝ ይሆን ? የአምባገነኖች ጡጫ እየደቆሰን ረሃብ በየዘመኑ የሚቆላንስ እስከመቼ ነው? በእውነቱ በሀሳብ ብዙ ባከንኩ አገኝለት ዘንድ ግን መልስ አጣሁ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እና የኢትዮጵያ ህዝብ መልስ አጥተው አያውቁም እና ተስፋዬ ፈፅሞ አይመክንም፡፡ እናም ያገባናል ለሚሉ ሁሉ እላለሁ የኢትዮጵያ ገፅታ የሚገነባው በየሰርጡ በጠኔ የሚሞቱ የወገኖችን እሬሳ በመደበቅ እንዳልሆነ ካሳለፍናቸው ክፉ ጊዜያት ተምረን ባለን አቅም ተረባርበን ወገኖቻችንን ለመታደግ እንበርታ እላለሁ…!!! በአዲስ አበባ፤ በባህር ዳር፤በአርባ ምንጭ፤ በጎንደር፤ በደሴ፤ በአዳማ፤ በአዋሳ፤ በወላይታ ህዝብ በሚንቀለቀል የለውጥ ፍላጎት ድምፁን ባሰማባቸው ሰላማዊ ሰልፎች… ‹‹ኢህአዴግ ከታሪክ ይማር፤›› ‹‹አምባገነኖች ባሉበት ሀገር የጀግና ሞቱ እስር ቤት ነው ፤›› ‹‹ታጋይ ይታሰራል ትግሉ ይቀጥላል፤ ›› ‹‹ እጃችን ባዶ ነው እነዚህ አምባገነኖች ነገ አሸባሪ ይሉናል›› ፤ ‹‹እመነኝ ደርግ ይወድቃል ኢህአዴግም ይወድቃል›› ማለታችንን ….. በእርግጥም ልክ ነበርን፡፡ ዛሬ አሸባሪ ተብለን ከትግል አጋሮቼ ከዳንኤል ሺበሺ ፤አብርሃ ደስታ ፤ የሺዋስ አሰፋ ፤አንዷለም አራጌ፤ ተመስገን ደሳለኝ ፤እስክንድር ነጋ ፤ ወዘተ…. ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር የነፃነት ቀንን እየናፈቅን በእስር ቤት አለን ፡፡ የፍርድ ቤት ድራማውም ተጠናክሮ ቀጥሏል ፍርድ ቤቶችን ከጀርባ ቆመው የሚዘውሩ በቀጭን ትዕዛዝ ማረሚያ ቤቶችን የሚያሽቆጠቁጡ፤ በፍትህ ስም የሚቀልዱ ፓርቲዬን ያፈረሱ፤ የህዝቤን ተስፋ ለማምከን ቀን ከሌት የሚደክሙ የካዛንቺሱ መንግስቶች እጃቸው የሚያጥርበትን ቀን አብዝተን እንናፍቃለን ፡፡ በእውነት እላለሁ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ ክፉን አልፈራም !!!

Wednesday, November 18, 2015

አገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሽልማት አሸናፊ “ሽብርተኛውን“ ተዋወቁት::በማያውቀው ክስ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን2 ይገኛል፡፡

አብርሃም ሰለሞን
አብርሃም ሰለሞን ይባላል ፡፡ በነ ዘላለም ወርቃለማው የክስ መዝገብ ከአራቱ የፓለቲካ አመራሮች በተከሰሱበት መዝገብ ስድተኛ ተከሳሽ የሆነው አብርሃም ሰለሞን መምህር ነበር ፡፡ አብርሃም ከመታሰሩ በፊት ቤተል ትምህርት ቤት መምህር ነበር ፡፡ በሞያውም የፈጠራ ስራዎች ላይ ማተኮር ይወድ ስለነበር አገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሽልማት አሸናፊ በመሆን ከተመረጡ መምህራንም መካከል አንዱ ነው ፡፡ነሃሴ ላይ ከታሰረ በኋላ ጥቅምት ላይ በተደረገው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ሽልማት ተሸላሚ በመሆኑ በጥቅምት ወር በተደረገው የሽልማት ስነስርአት እናቱ ወክለውት ሽልማቱን ተቀብለዋል ፡፡ ይህ በሽብር የተከሰሰ ወጣት አስተማሪ አይሲቲን በቀላሉ እና በሚገባ መልኩ ማስተማር የሚረዳ የፈጠራ ውጤት ባለቤት በመሆኑ ነው ሽልማት ያገኘው ፡፡ የሽልማቱ ቲሸርት እና ሜዳልያን ይዘው ሊጠይቁት የሄዱት እናቱ ሜዳልያውን ማስገባት ባይችሉም ቲሸርቱን አስገብተውለት ተመልሰዋል ፡፡ በማስተማር እና በፈጠራ ስራ የተሰማራው ይህ መምህር አንድም እውነተኛ ሽብተኛ ተከሶበት በማያውቀው ክስ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን2 ይገኛል፡፡ በእርሱ የመምህርነት ደሞዝ ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦቹም እሱን ቅሊንጦ ድረስ እየሄዱ በመጠየቅ እየተንከራቱ ይገኛሉ ፡፡

ቢያንስ ኢንተርኔት ላይ ሼር በማድረግ የማናውቃቸው ብዙዎች ለሚከፍሉት ዋጋ እውቅናን እንስጥ


Monday, November 9, 2015

የአ/አበባ ሀ/ስብከት በቀጣይ ብክነት ላይ – “ፓትርያርኩን ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው” በሚል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ኾነ!

  • የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በዋና ሥራ አስኪያጅነት በመቀጠሉ የምስጋና ሰርፕራይዝ” ነው
  • ያልታቀደው ወጪ፣ የፓትርያኩን የመኖርያ ቤት ዕቃዎች ለመቀየር መዋሉ ተነግሯል
  • ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩን የማስተዳደር ሓላፊነት ያለው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አያውቀውም
  • የሀ/ስብከቱ ሒሳብ፣ ያለተቆጣጣሪና ያለዕቅድ በየማነ ዓምባገነንነት እንዲባክን ተፈርዶበታል
2007Yek
በወሬ እና በይስሙላ አካሔዶች የተሳሳተ ምስል እየፈጠረ ራሱን እንደ ለውጥ አራማጅ እና መሪ በመስበክ የሥልጣን ወራቱን እያራዘመ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “ፓትርያርኩን ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው” በሚል ከሀገረ ስብከቱ ሒሳብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዲኾን ማድረጉ ተገለጸ፡፡
“የፓትርያርኩን የተጓደሉ የመኖርያ ቤት ዕቃዎች ለማሟላት እና ለመተካት” በሚል ከሀገረ ስብከቱ ተቀማጭ ብር 586‚000 ወጪ የተደረገ ሲኾን ግዥው አስቀድሞ ያልታቀደና በጀትም የተያዘለት እንዳልነበር ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በተደረገው የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባ፣ አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት መኾኑን በመጥቀስና “ሥራ አስኪያጃችንን ስላስቀጠሉልን ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው” በሚል ግፊት አስቀድሞ ተሰብስቧል በተባለው ፕሮፎርማ መሠረት ግዥው በተጠቀሰው ወጪ እንዲካሔድ መወሰኑ ተመልክቷል፡፡
እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ፣ እንዲህ ባሉ ግምታቸው ከፍተኛ በኾኑ ወጭዎች የፈራሚው ሊቀ ጳጳሱ አልያም የፓትርያርኩ ፈቃድና መመሪያቢያስፈልግም ግዥው በዋናነት በሥራ አስኪያጁ አመንጪነትና በአድርባይ ሓላፊዎች ግፊት በታቀደ “ሰርፕራይዝ” በመከናወኑ፣ የሀገረ ስብከቱ ተቀማጭ ሒሳብ ያለበላይ ተቆጣጣሪ በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አማሳኝ እና ዓምባገነናዊ አካሔድ እየባከነ ለመኾኑ አረጋግጧል፡፡
“አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ስለኾነ” የሚለው የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ ተነሥቶ ውሳኔውን ሕጋዊ ለማስመሰል ቢጠቀስም ክፋቱ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሥልጣን ማራዘሚያ መርፌ መኾኑ ነው፤” ያሉ የመረጃው ምንጮች፣ የቅዱስነታቸውን መኖርያ ጨምሮ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩን በባለቤትነት የማስተዳደር ሓላፊነት ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እንደኾነና በጉዳዩ እንዳልተማከረ፣ የሚያውቀውም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
“የፓትርያርኩን መኖርያ ቤት ማሟላት የቤተ ክህነቱ ድርሻ ነው”  በሚል ለተነሣው ሐሳብም “ከእዚያ ጋር መነካካት አያስፈልግም፤ የራሱ ጉዳይ” የሚሉ በእብሪት የተሞሉ ምላሾች ከአድርባዮቹ ሓላፊዎች መሰጠታቸው ታውቋል፡፡
ግዥውን እንዲያከናውን በተቋቋመው ሦስት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ባሉበት ኮሚቴ፣ ለየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ቅርበት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የፓትርያርኩ ረዳት የኾኑት መነኮስ እንዲጨመሩ መደረጋቸው፣ ‘ሰርፕራይዝ ነው’ የተባለውን ምስጋና አወሳስቦታል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከጥቅምት 25 ቀን ጀምሮ ወደ ምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት መጓዛቸውን ተከትሎ፣ “ከዓዲ ግራት መልስ ሳያውቁ ቤታቸው ተቀይሮ ማግኘት አለባቸው” በሚል ከኢትዮ ሴራሚክስ፣ ከግሎሪየስ፣ ከአዲስ ዲኮር፣ ከዋሪት፣ ከዋው፣ ከዴሉክስ ፈርኒቸርስ በርካታ የግል መገልገያ ዕቃዎች ተሸምተው በጨረታ ያሸነፈ ነው በተባለው ድርጅት እንዲገጠሙ ተደርጓል፡፡
በተከናወነው ግዥ÷ የሳሎን፣ የመኝታ እና የመታጠቢያ ቤት እንዲኹም የመመገቢያ አዳራሽ ዕቃዎች የተካተቱ ሲኾን ከእነርሱም መጋረጃ እና የወለል ምንጣፎች፤ ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች፤ አልጋ እና ፍራሽ፤ ጃኩዚ እና ቴሌቭዥኖች እንደሚገኙበት ተገልጧል፡፡
የፓትርያርኩ የመኖርያ ቤት መገልገያዎች፣ ከአያያዝ ጉድለት ይኹን ከጊዜ ብዛት “አርጅተዋል፤ ቆሽሸዋል፤ በልዘዋል፤ ተነቃቅለዋል” ቢባል እንኳ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ተጠሪ እንደ መኾኑ መጠን የገንዘብ እንቅስቃሴውን ማወቅና በጉዳዩም መማከር ነበረበት፡፡
ባለመደረጉ፣ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ያልታቀደና ያልተፈቀደ የሥልጣን ማራዘሚያ ‘ሰርፕራይዝ’፣ በአወዛጋቢ የሥራ አስኪያጅነት ምደባው ሳቢያ ካለፈው ዓመት የካቲት ወዲኽ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋር ተቃውሶ የቆየውን መዋቅራዊ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያባብሰው ተጠቁሟል፡፡
በርግጥ፡-
  • ከሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ጋር በዋና ጸሐፊነት ደርቦ በያዘው የገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ደብር፣ ያለሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ያለሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ በሕገ ወጥ የዲዛይን ክለሳ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ ልዩነት ያለበትን ሕንፃ በማስቀጠልባካበተው ዳጎስ ያለ ሀብት ቀጣይ የቢዝነስ ፕላኑን እያማተረ ላለው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
  • ያለሊቀ ጳጳሱ መመሪያና ያለአስተዳደር ጉባኤው ውሳኔ÷ በአጥቢያ ሠራተኞችና ካህናት ዝውውር፣ ቅጥር እና የ“ጠብቀኝ፣ አትንካኝ” መደበኛ አምኃዎች ምዝበራውን ላጧጧፈው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
  • ከአወዛጋቢ ምደባውና ከሙስና ወንጀሉ ጋር በተያያዘ፣ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅት የተፈጠረበትየተጠያቂነትና የመወገድ ስጋት አልፎኛል በሚል በቀጣይ የበርካታ አድባራት አለቆችን በማዘዋወር ወንጀሉን ለመሸፈንና ምዝበራውን ለመቀጠልለቋመጠው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
የፓትርያርኩ የብር 586‚000 የሥልጣን ማራዘሚያ እና የምስጋና ሰርፕራይዝ ወጪ ላያስደነቅ ይችል ይኾናል፤ ሀገረ ስብከቱ ግንበፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኝ ብሎጎች ጭምር በሚታገዘው የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ከተግባር የራቀ የለውጥ አራማጅነትና መሪነት ዲስኩሩ ሽፋን፤ እንዲኹም ሕግና ደንብ በማይገዛው አማሳኝና ዓምባገነናዊ አካሔዱ በቀጣይ ብክነት እንዳለ ተረጋግጧል!!