Thursday, August 20, 2015

አክራሪና አሸባሪዉ ኢህአዴግ ወይስ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት? ርዕዮት አለሙ

ልጆች ሆነን "እከሌ (እከሊት) አክራሪ ነዉ (ናት) " ሲባል ይሰጠን የነበረው ትርጉም እና አሁን አክራሪነት እየሰጠ ያለው ትርጉም ለየቅል ይመስለኛል፡፡ ያኔ አንድ ሰው በአክራሪነት ሲጠራ ከብዙሃኑ በተለየ ሁኔታ ሃይማኖቱን ወይም የሚያምንበትን አንዳች ነገር አጥብቆ መያዙን እና በሚያምንበት ነገር ላይ የማይደራደር መሆኑን ከማሳየት አልፎ የአሁኑን አይነት አሉታዊ ትርጉም አይሰጥም ነበር፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ያኔ ቃሉን እረዳበት ከነበረዉ ትርጉም ብዙም የራቀ ፍቺ አያቀርብም፡፡ በ1993 ዓ.ም የካቲት ወር የተዘጋጀዉ ይኸዉ መዝገበ ቃላት አክራሪ ለሚለዉ ቃል የሚሰጠዉ ፍቺ "በሚከተለዉ እምነትና አስተሳሰብ ውስጥ ፍፁምነት ሊኖር ይገባል ብሎ የሚያምንና የቆየውን እምነትና አስተሳሰብ ከዘመናዊው ሁኔታ ጋር ማስተካከል እና ማጣጣም የማይፈልግ አጥባቂ (ሰዉ)" የሚል ነዉ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የቃሉ ፍቺ እየተቀየረ መጥቶ አሁን
ያለውን እጅግ አሉታዊ የሆነ ገፅታ ይዟል፡፡
የህግ ባለሙያው ተማም አባቡልጉ የካቲት፣ 3 2007ዓ.ም በወጣው ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ "አክራሪ ሰዎች እነማን ናቸው?" በሚል ርዕስ ባስነበቡት ፅሁፋቸዉ "የራሱን ዘር፣ ሃይማኖትና ቡድን ጥቅም ሌሎችን በመጉዳት ጭምር ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀስ ወይም ከማስጠበቅ የማይመለስ" ሰዉ እንደሆነ አክራሪ የሚባለዉ ገልፀዋል፡፡
የዚህ ፅሑፍ አላማ አሁን እየተግባባንበት ካለው ፍቺ አንፃር "የአክራሪነትና የአሸባሪነት ባህሪ የሚንፀባረቀው በቅርቡ በተፈረደባቸው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ወይስ በከሳሹ መንግስት?" የሚላውን ጉዳይ መፈተሽ ይሆናል፡፡

የኢህአዴግ የምናብ ቀበሮዎች
ኢህአዴግ እኔን ጨምሮ በርካታ ከሽብር ጋር ሊገናኝ የማይችል ማንነት ያለንን ዜጎች የአሸባሪነት ስም ሰጥቶናል፡፡ ይሄን ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ብዙዎቻችሁ የምታዉቁት የውሸታሙ እረኛ ታሪክ ነዉ፡፡ እንደምታስታውሱት ሌሎችን በማታለል የሚዝናናው ዉሸታሙ እረኛ ቀበሮ መጥቶ በጎቹን እየበላበት እንደሆነ አድርጎ የድረሱልኝ ጥሪ በጩኸት በማቅረብ አላፊ መንገደኞችን ይሰበስባል፡፡ መንገደኞቹ ለእርዳታ ሲመጡ ታዲያ ቀበሮው በገሀዱ አለም ያለ ሳይሆን የእረኛው የምናብ ዉጤት መሆኑን ይረዱና እየተበሳጩ ወደየመንገዳቸው ይመለሳሉ፡፡ ኢህአዴግም "አክራሪ ደረሰብን ፤ አሸባሪ መጣብን" እያለ አደንቋሪ ጩኸቱን ለቁጥር በሚያዳግት መልኩ በተደጋጋሚ አሰምቷል፡፡ ጩኸቱን ሰምተው ስለሁኔታው ለማወቅ የሞከሩትን ሁሉ ግን የጠበቃቸው እንደዉሸታሙ እረኛ የምናብ ቀበሮ ሁሉ የውሸት አክራሪና አሸባሪ ነዉ፡፡
የምናብ ቀበሮ የሚበላው በግ እንደሌለ ሁሉ የምናብ አክራሪና አሸባሪም የሚያወድመው ንብረትም ሆነ የሚያጠፋው የሰው ህይወት የለም፡፡ እስክንድር ነጋና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችና ጦማሪያንን አሸባሪ ሊያሰኝ የሚችል ምን አደረጉ? አንዷለም አራጌ እና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ምን አጠፉ? ምንም!

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የኢህአዴግ የምናብ ቀበሮዎች ናቸው፡፡ ኡስታዝ አቡበከር አህመድም ይሁን ሌሎቹ የኮሚቴ አባላት አክራሪም ሆነ አሸባሪ ለመባል የሚያበቃ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ይልቁንም መንግስት በሃይማኖታቸው ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እምነቱን ለመበረዝና ለመከለስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም እጅግ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲጠይቁ የነበሩ በህዝበ ሙስሊሙ የተመረጡ የአላማ ሰዎች ናቸው፡፡ ለመረጣቸዉ ህዝብና ለሃይማኖታቸው ታማኝ ሆነው መገኘታቸው ግን ለኢህአዴግ ስላልተስማማው እንዲያስራቸው ብሎም ለመስማት የሚከብድ አሰቃቂ በደሎችን እንዲፈፅምባቸው ምክንያት ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በስህተት ያሳየው የአንደኛ ተከሳሽ የአቡበከር አህመድ እጆች በካቴና ታስረው ሲመረመር የሚያሳየው አሳዛኝ ምስል የተመለከተውን ሁሉ ልብ የሚያደማ ነበር፡፡ በሁኔታዉ ልባቸው የተነካ ሙስሊም ወገኖቻችንን
አቡኪ ወንድሜ የእስልምና ብርሃን 
ሁኔታህን አይተን ሁላችን አነባን
ብለው እንዲያዜሙ ያስገደደ ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኮሚቴዎቹ ከታሰሩበት አሰቃቂ ቦታም ሆነው ሰላማዊ የሆነው ጥያቄ መንግስት በሚወስዳቸው ያልተገቡ የአፈና ምላሾች ሳቢያ ሌላ መልክ እንዳይዝ በጎ መልዕክት ከማስተላለፍ ወደኋላ አላሉም፡፡ ኮሚቴዎቹ በዚህ መጠን ከህዝበ ሙስሊሙ አልፈዉ ለሀገር ሰላም ቢጨነቁም ውሸታሙ እረኛ ግን የተለመዱ የሀሰት ዶኪመንተሪ ፈልሞችን በማቅረብ ስማቸውን ለማጥፋት ሲታትር ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ በቅርቡ ከሰባት እስከ ሃያ ሁለት አመታት የሚደርስ ፍርድ ቀኝ እጁ በሆነው ፍርድ ቤት በኩል አስተላለፈባቸው፡፡ ይህ አስገራሚ ፍርድ በሚተላለፍበት ወቅት ግን ኮሚቴዎቹ በጀግንነት ቆመው እንባ የሚራጩ ዘመድ ወዳጆቻቸውን ሲያፅናኑ እንደነበር ችሎቱን የተከታተሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አስቀድመው በነበሩ ችሎቶች ላይ "እዚህ የቆምነው ፍትህ እናገኛለን በሚል እምነት አይደለም፡፡ ለታሪክ ምስክር ለመሆን እንጂ" በማለት እንደገለፁት ከካንጋሮው ፍርድ ቤት የሚጠብቁት ፍትህ ባለመኖሩ የተሰጣቸው ፍርድ እንደማያስደነግጣቸው ግልፅ ነው፡፡
የኮሚቴዎቹ አባባል ኔልሰን ማንዴላ ያልተገባ ስም ተሰጥቷቸዉ ለፍርድ በቀረቡበት ወቅት የተናገሩትንና የግል የህይወት ታሪካቸውን ባሳተሙበት መፅሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለዉን ሃሳብ ያስታዉሰኛል፡፡

“ይህ የፍትህ ስርዐት ጥፋተኛዉ ንፁሑን በህግ ፊት እንዲያቀርበዉ ጉልበት የሚሰጠው በመሆኑ ትልቅ ስጋት ዉስጥ ይከተኛል፡፡ የፍትህ ስርዐቱ ልክ ያልሆነዉ ልክ የሆነዉን እንዲከስና ማስቀጣት እንዲችል የሚያደርግ ነው... በመሆኑም ፍትሃዊና ተገቢ ፍርድ አላገኘም፡፡”
ያኔ ኔልሰን ማንዴላ አስቀድመው እንደተናገሩት የአፓርታይድ መሪዎቹ የሚያሽከረክሩት ፍርድቤት ያልተገባ ፍርድና የወንጀለኛነት ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ ዛሬም ኮሚቴዎቹ ኢህአዴግ በሚያሽከረክረው ፍርድቤት አማካኝነት ከማንዴላ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ፍርድና ተመሳሳይ የሆነ ስያሜ አግኝተዋል፡፡ "አሸባሪነት" ዛሬም እንደትላንቱ ሁሉ አምባገነኖች የሚቃወሟቸውን ንፁሃንን የሚመቱበት ዱላ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
አክራሪዉ ኢህአዴግ ነዉ!
የኢህአዴግ ባላስልጣናት አክራሪነት ከሱ ሌላ የሆነ ቡድን ወይም ማንነት እንዲኖር የማይፈቅድ እንደሆነና "ለልማታችን እና ለዲሞክራሲ ግንባታችን" ዋነኛ ጠር መሆኑን ሁሌም እንደነገሩን ነው፡፡ ከአባባሉ ተነስተን አክራሪ ስንፈልግ ውለን ብናድር የምናገኘዉ ትልቁ አክራሪ ግን እራሱ ኢህአዴግ ሆኖ ይገኛል፡፡
ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሌላ ርዕዮተ አለም በሀገራችን እንዳይኖር አይደለም እንዴ የተለየ መስመር የሚከተሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያፈርሰው? በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መፅሔቶች የመዘጋታቸውና ጋዜጠኞቹ የመታሰርና የመሰዳደቸው ምክንያትስ እርሱ ከሚቆጣጠራቸው ዉጪ የሆኑ ሚዲያዎች እንዳይኖሩ ከመፈለግ የመጣ አይደለምን? የደሃ ሀገራችንን አንጡራ ሃብት እንደ ሃኪንግ ቲም ላሉ የጣልያን ተቋማትን የሚከሰክሰዉ ሁሉን ለመቆጣጠር ባለዉ ክፉ አባዜ ምክንያት መሆኑን መች አጣነዉ? የትምህርትም ሆነ የስራ እድል የኢህአዴግ አባል ካልተሆነ ለማግኘት የጠበበው ከኢህአዲግ አክራሪ ባህሪይ የመነጨ መሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ ሌሎች ብዙ የኢህአዲግ አክራሪነት መገለጫዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማጠቃለል ያህል አንዱን ልጥቀስ
በሜታ ሮቢ ወረዳ አስተዳደር የወራቦ ቀበሌ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑ አስራ አራት ግለሰቦች "በ2007ዓ.ም በተካሄደዉ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሲደግፉ ነበር" በሚል አስገራሚ ምክንያት የተነሳ ማናኛውንም የህግና የአስተዳደር አገልግሎቾችን ማግኘት እንዳይችሉ በቀበሌ አስተዳደሩ ለሚመለከተው ሁሉ ስማቸዉ ተዘርዝሮ ተፅፏል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው እነዚህን ግለሰቦች ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየደረሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የችግሩን ምክንያት ሲያስረዱም "እነዚህ ታጋዮቻችን ህዝቡ መድረክን እንዲመርጥ ምን ሲሰሩ እንደነበር ስለሚያዉቅ አሁን እየወሰደ ያላው የበቀል እርምጃ ነው" ብለዋል፡፡ በዚህ መጠን ከእርሱ ሌላ እንዳይኖር የሚፈልገውና ኖሮ ሲገኝ ደግሞ ተሸብሮ ህዝቡን የሚያሸብረው ኢህአዴግ የማይገባቸውን ሰዎች አሸባሪ እና አክራሪ ሲል አፉን ያዝ እንኳን አያደርገውም፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ያልተገባ ስም የሰጣቸዉ ሙስሊም እህቶቻችን ቢቸግራቸዉ እንዲህ በማለት ሊያርሙት ሞክረዉ ነበር፡፡
¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬
የሂጃቡ ነገር ከላይ ከፈጣሪ 
የኒቃቡስ ነገር ከላይ ከፈጣሪ
ልባል አይገባም አክራሪ አሸባሪ
¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬¬
የኮሚቴዎቹ እስርና ፍርድ ምን ሊያስከትል ያችላል?
ገዢው ፓርቲ ጥያቄዎችም ሆነ ተቃዉሞዎች ሲነሱበት ራሱን ከመመርመር ይልቅ በድፍረት ድምፃቸውን ያሰሙ አካላትን ማሰርን ይመርጣል፡፡ በዚህም እፎይታን የሚያገኝ ይመስለዋል፡፡የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም ላይ ያደረገዉ ይህንን ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ አካሄዱ የተመኘውን እፎይታ ሊያስገኝለት ይቅርና ለሀገር የሚተርፍ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ጉዳዩን በጥልቀት የተከታተሉ ወገኖች ይገልፃሉ፡፡
ከነዚህ ወገኖችአንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ሀይለመስቀል በሸዋምየለህ በቅርቡ ገበያ ላይ በዋለውና "የሀይለማርያም እዳ እና የሙስሊሙ ትግል" በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መፅሐፉ ውስጥ በርካታ በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ እንደገለፀው ኢህአዴግ የሙስሊሙን ጥያቄ ለማፈን እየተጓዘበት ያለው መንገድ እጅግ አፍራሽ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ከአፍራሽ ውጤቶቹ አንዱ ደግሞ "ኢህአዴግ እየተከላከልኩት ነው የሚለው ፅንፈኝነት መፈጠር" ሊሆን እንደሚችል መፅሐፉ ያስረዳል፡፡ ዶ/ር አባድር ኢብራሂም ADDIS STANDARD በተሰኘ ወርሃዊ መፅሔት የዚህ ወር እትም The unfair trial of Muslim Leaders ; why it undermines counter terrorism in Ethiopia በሚል ርዕስ ባቀረቡት ፅሁፋቸው ውስጥም ተመሳሳይ ስጋት እናገኛለን፡፡
ዶ/ር አባድር ኮሚቴዎቹ ላይ የተሰጠውን የጥፋተኝነት ዉሳኔ መነሻ በማድረግ ባዘጋጁት በዚህ ፅሁፋቸው የተላለፈው ውሳኔ የፍትህን መክሸፍ ከማሳየቱም በላይ እነዚህ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ወደፊት ከሚመጣ የሽብር አደጋ የመስዕዋት ጠቦት ሆነው ሊያድኑን አለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ ዶክተሩ ኮሚቴዎቹ ላይ የተላላፈዉ ውሳኔ እንደዉም የሽብር ስጋቱን እንደሚጨምር አምስት መከራከሪያዎችን በማቅረብ ይሞግታሉ፡፡ 
እኚሁ የህግ ምሁር ከመከራከሪያዎቹ በአንዱ እንዳብራሩት ኮሚቴዎቹ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ እጅግ ተሰሚነት ያላቸዉ መሪዎች እንደመሆናቸውና በፀረ ሽብር ትግሉ አገላለፅ "ለዘብተኛ" የሚባሉ ስለሆኑ አክራሪነትን ለመከላከል ግንባር ቀደም አጋር ሊሆኑ የሚችሉ ነበሩ፡፡ ኢህአዲግ እነዚህን ትልቅ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ መሪዎችን በመክሰስና በማሰር እዋጋቸዋለሁ የሚለውን አክራሪ ድርጅቶች የቤት ስራ እንደሰራላቸው ዶክተሩ በፅሁፋቸው ይገልፃሉ፡፡ ምክንያቱን የሚያብራሩትም እንደነ አቡበከር አይነቶቹ ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍረታት የሚታትሩ ሙስሊም መሪዎች ባላቸው ተቀባይነት ፅንፈኛ ድርጅቶች ቅቡልነት እንዲያጡ በማድረግና የድርጅቶቹን ትምህርቶች ሊገዳደር በሚችል የሃይማኖቱ ትምህርት በመምታት እስልምናን ሽፋን አድርጎ የሚመጣን የሽበር አደጋ ለመከላከል የነበራቸዉን አቅም በመጥቀስ ነው፡፡ ዶክተሩ በሌላኛው መከራከሪያቸው ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ጥያቄያቸዉን ለማቅረብ በሞከሩ ሙስሊሞች ላይ መንግስት እየፈፀማቸዉ ባሉ በደሎች ሳቢያ አመፅ-አልባ ትግሉ ጥያቄ ውስጥ መግባቱና ሰዎች ወደሌላ አማራጭ ለማየት መገደዳቸዉ እንደማይቀር ያስገነዝባሉ፡፡
ጋዜጠኛ ሀይለመስቀልም ሆነ ዶ/ር አባድር ይሄ ትልቅ ሀገራዊ ችግር የሚያመጣው ኪሳራ አሳስቧቸው መፍትሄ ፍለጋ ላይ ታች ቢሉም ኢህአዴግ ግን አሁንም ከመጥፎ ድርጊቱ አልታቀበም፡፡ በትላንትናው ዕለት እራሱ ኮሚቴዎቹን ለማስፈታት ተንቀሳቅሳችኋል ያላቸዉ ሃያ የዕምነቱ ተከታዮች ላይ ክስ እንደመሰረተ በማህበራዊ ድረገፆች እያነበብን ነው፡፡ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅትም የአዳማ ሙስሊም ተማሪዎችን ጨምሮ በተመሳሳይ ክስ በርካታ ሙስሊሞች ይታሰሩ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ስህተቱን በስህተት ለማረም የሚያደርገዉ እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ እንቅስቃሴ መገታት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በሀሰት ቀበሮ እየተባሉ ፍዳቸዉን የሚያዩ ንፁሃን ወገኖቻችን ጉዳይ አሳስቦን በአንድነት መቆምና ገዢውን ፓርቲ መታገል ካቃተን ነገ እዉነተኛ ቀበሮዎች ቢመጡ የምንመክትብት ጉልበት አይኖረንም፡፡ ለአሁኑ ግን ለእኔ የታየኝ አደገኛ ቀበሮ ኢህአዴግ ራሱ ነዉ፡፡

No comments:

Post a Comment