በስልክ ተደውሎ የአሲምባ ፍቅር የሚል መጽሃፍ ፈልጊና አንብቢ የእህትሽን ታሪክ የያዘ መጽሃፍ ነው ስባል ልክ
በህይወት መጣችልሽ የተባልኩ መሰለኝ ሲቃ እያነቀኝ ወደ መጻህፍት ቤት ገሰገስኩ ስደርስም ለመጠየቅ አቃተኝ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ ከንፈሬ ሁሉ እየተርበተበተ
መጽሃፍ ሻጯን ጠየቅኋት አለ ስትለኝ ልስማት አልኩና ደነገጥኩ እንደገና ከዚያም እራሴን ተቆጣጥሬ መጽሀፉን ተቀብየ ሳም አደረግሁት ሴትዮዋ በመገረም አየችኝ፡፡
ደፍሬ ግን ለማንበብ አልችል አልኩኝ ደስታ ይሁን ሀዘን አላወቅሁም ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ተሰማኝ ከዚያም ለ4 ቀናት ያክል አመመኝ እና ተኛሁ እንደድርሳነ
ሚካኤል አቅፌው ተኛሁ ከዚያም እራሴን አረጋግቼ ማንበብ ጀመርኩ::
ምንም እንኳ የምትወዳቸውን ጓደኞችህን እና ያሳለፍከውን የውጣ ውረድ ዘመን እያሰብክ ሰላም ባይሰማህም ለእናትና አባትህ እንኳን እግዚአብሔር አተረፈላቸው ከነሱም አልፎ ለእኔና እኔን መሰል ያለ ታሪክ የቀሩ ቤተሰቦች ላሏቸው ሲል አምላክ እንኳን ከዚህ ቀን አደረሰህ፡፡ እህቴ መሞቷ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ተካፋይ ባለመሆ ኗ አእምሮዬ ቆስሎ ይኖር ነበር ፡፡
በአፈ ታሪክ ታጋዮች ሁሉ ጀግንነቷን ያላትን ጥሩ ስነምግባር ይተርኩልኛል ነገር ግን የታሪክ መዝገብ ላይ አላሰፈሯትም፡፡ ከከተማ ሳይወጡ በቀይ ሽብር
የተረሸኑት ደርግ እንደተደመሰሰ በቤተክርስቲያን መቃብር ቤት ተገንብቶ ከተረሸኑበት አጽማቸው ወጥቶ በክብር እንደገና ተቀበሩ እናም የቀይ ሽብሮች መቃብር ቤት ሲታይ ቤተሰቦቻቸው አልቅሰውም ሆነ ስቀው የልጆቻቸውን ታሪክ ያወሳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በበረሃ የተሰውት ደግሞ የሰማእታት ሃውልት ተብሎ በተገነባው ውስጥ የአንድ ታጋይ ስሙና ትውልዱ የሰራው ታሪክ የተሰዋበት ቦታ ሁሉ በዝርዝር ይገኛል፡፡ የእኔ እህት ግን ውሻ ስታባርር የሞተች ይመስል የታሪክ መዝገብ ላይ ስሟ የለም አንዳንድ ታጋዮችን ሳነጋግራቸው እሷ የተሰዋችው ብአዲን ሳይመሰረት በኢህአፓ ዘመን ነው ይሉኛል ኢህአፓ የውጭ ዜጋ ይመስል፡፡ እናም አእምሮዬ ሲደማ የቆየበት ታሪክ ዙሮ በአሜሪካ ሲመጣ ከቁስሌ ተፈወስኩ፡፡
ድርብ ምናለ
No comments:
Post a Comment