Thursday, April 14, 2016

አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁልቁል መምዘግዘጉን አስታወቀ

(ሳተናው) አለም አቀፉ የሞኒታሪ ፈንድ የአገራትን ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በማስመለከት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁልቁል መምዘግዘጉን አስታውቋል፡፡

ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በ30 ዓመታት የቅርብ ግዜ ታሪኳ ውስጥ አስተናግዳው የማታውቀውን አይነት ከፍተኛ ድርቅ በማስተናገዷ 100 ሚልዮን ከሚገመተው ህዝቧ አምስት ከመቶ የሚሆነው የምግብ እርዳታ የሚፈልግ ሆኗል ያለው አይ ኤም ኤፍ ለዚህም 1.4 ቢልዮን ዶላር መጠየቁን አስታውሷል፡፡
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ፈጣን የተባለ የኢኮኖሚ እድገት(10.2%)ማስመዝገቧን የገለጸው ተቋሙ በዚህ ዓመት ኢኮኖሚው ወደ 4.5% ማሽቆልቆሉን በአግራሞት አስፍሯል፡፡የኢኮኖሚው እድገት በአገሪቱ የተፈጠረውን ድርቅ ተከትሎ በዚህ አመት 8.1% እንደሚሆን ተገምቶ ነበር ያለው አይ ኤም ኤፍ በ2017 የኢኮኖሚ እድገቱ 7 ከመቶ ይሆናል ተብሎም ተተንብዮ ነበር ብሏል፡፡
አይ ኤም ኤፍ በሪፖርቱ ከአፍሪካ አገራት መካከል አይቮሪ ኮስት፣ኬንያ፣ሩዋንዳና ሴኔጋል ከ6-7 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት በያዝነውና በቀጣዩ ዓመት እንደሚያስመዘግቡ ትንበያውን አስቀምጦላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከወር በፊት የመንግስታቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት ላለፉት አስርት አመታት እንደ ዶግማ ተይዞ የነበረው የሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ እድገት ገለጻ በዚህ አመት እንደማይኖር በማውሳት የኢኮኖሚ እድገቱ በአንድ ዲጂት እንደሚሆን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በአንጻሩ የጠቅላይ ሚንስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ዶክተር አርከበ ዕቁባይ የኢኮኖሚ እድገቱ ዘንድሮም ሁለት ዲጂት እንደሚያስቆጥር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪ

No comments:

Post a Comment